ኦርቶዶክሳውያን ድረ-ገጾችን ለማዘጋት እየተዶለተላቸው ይገኛል

(አንድ አድርገን ሐምሌ 25 ፤ 2005 ዓ.ም)፡- ዘመኑን ዋጁ እንዲል ቃሉ ከጊዜ ወዲህ ድረ-ገፆች መረጃን ለምዕመናን እያስተላለፉ ይገኛሉ ፤ የአምስት ዓመት እድሜ ያስቆጠረችው በእድሜ አንጋፋዋ “ደጀ ሰላም”ን ጨምሮ ፤ አንድ ዓመት በቅጡ ያልሞላት “አንድ አድርገን” ፤ ደቂቀ ናቡቴና አሐቲ ተዋህዶን የመሰሉ ገጾች የቤተክርስትያንን መረጃዎች የመናፍቃንን አካሄዶች በየጊዜው በማውጣት ይታወቃሉ ፤ ከዚህ በተቃራኒ በሌላኛው ጎራ የቆሙ የተሀድሶያውያን እና የመናፍቃን ገጾች ያለመታከት ቤተክርስትያኒቱን ለመከፋል ያለ እረፍት እየሰሩ ይገኛሉ ፤ “አባ ሰላማ”ና አውደ ምህረትን የመሰሉት ገጾች ውስጥ በሚገኙ እነሱን ከሚመስሏቸው ሰዎች ጋር በመሆን መረጃዎችን እየተቀባበሉ ምንፍቅናቸውን እና ኢ-ኦርቶዶክሳዊ የሆነ አካሄዳቸውን በጽሁፋቸው እየገለጹ ይገኛሉ ፤ የነዚህን ገጾች ጽሁፍ አይቶ እነ ማን እንደሆኑ ለማወቅ የተለየ ብልሀትን የጠለቀ ምርመራ ማድረግን አይጠይቅም ፤ ቅዱሳንን የሚዘልፉና  ገድላትን የሚያንቋሽሹ ጽሁፎቻቸው ምስክሮቻቸው ናቸው፡፡ ይህ በእንዲህ እያለ ደጀ-ሰላም እና አንድ አድርገን በኢትዮጵያ ውስጥ እንዳይነበቡ ቢደረግም እነዚህን የመሰሉ የተሃድሶያውያን ገጾችን ግን የደረሰባቸው የለም ፤ አሁን ደግሞ ይባስ ብሎ ከወደ አሜሪካ እነዚህን ገጾች እንዲታገዱ የሚጠይቅ ስብሰባ መደረጉን የአቋም መግለጫ መውጣቱን የሚያመላቱ መረጃዎች ወጥተዋል ፤ ከበስተጀር እየተዶለተላቸው ይገኛል ፤ እነርሱ አልገባቸውም እንጂ “አንድ አድርገን” እና “ደጀ ሰላም” በፌስ ቡክ ካልሆነ በስተቀር በቀጥታ የማይነበቡበት ደረጃ ላይ ደርሰዋል ፤ አንድ አድርገን በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ አሁን ለ3ተኛ ጊዜ እክል ገጥሟታል ፤ ከዚህ በፊት አንድ በአንድ እየተባለ ሁለት ገጾች ቢዘጉም አሁን ግን በተለዋጭነት መረጃ ለማስተላለፍ የምትተቀምባቸው 6 ገጾች በጠቅላላ ኢትዮጵያ ውስጥ እንዳይሰሩ ተደርገዋል ፤ ይህ ሁሉ ቢሆንም ከኢትዮጵያ ውጭ በቀን ቢያንስ በሺህ በሚቆጠሩ ሰዎች እንደምትጎበኝ የብሎጉ ስታተስ ይጠቁማል ፤ ከቀናት በኋላም እነርሱ መዝጋት ካልሰለቻቸው እኛ መክፈቱ ስለማይከብደን ተጨማሪ አማራጭ ገጾች እንደምንከፍት በዚህ አጋጣሚ ለመግለጽ እንወዳለን፡፡

እንደ “አንድ አድርገን” እምነት ካለው ተጨባጭ ሁኔታ በመነሳት የተሃድሶያውያን እና የመናፍቃንን አካሄድ መረጃዎች ሰዎች ዘንድ አድርሰናል ብለን አናምንም ፤ እስከ አሁን ከወጣው መረጃ እየሰበሰብንና እያጠናከር ያሉ ጉዳዮች ይበዛሉ ፤ የሐዋሳው ጉዳይ ዳግም ለመቀስቀስና ምዕመኑን ወደማያባራ ቀውስ ውስጥ ለመክተት በማሴር እነ ያሬድ አደመ ስራቸውን እየሰሩ ይገኛሉ ፤ ቅዳሴ ቤተክርስትያን እያስቀደሱ ወንጌሉን ደግሞ በአዳራሽ የሚል ፈሊጥ በመያዝ ለተግባራዊነቱ እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ ፤ ውስጦቻችን ተሰግስገው ያሉ አመቺ ጊዜ የሚጠብቁ ሰዎች ተበራክተዋል ፤ አሁንም በአንድም ይሁን በሌላ መንገድ ኦርቶዶክስ ቤተክርስትያን እና መናፍቃኑ አዳራሽ የሚመላለሱ ሁለቱም ጋር የሚያገለግሉ ሰዎች ተበራክተዋል ፤ በተመሳሳይ አንዳንድ ከተማዎች ላይ የቅባት እና የጸጋ አስተምህሮ ያላቸው ሰዎች ምዕመኑን እያመሱት ይገኛሉ ፤ ከነዚህ በተጨማሪም አሁን የማናመላክተው  በርካታ ነገሮችም አሉ ፤ እነዚህ ሁሉ ጉዳዮች ወደፊት ጊዜውን ጠብቀው የሚፈነዱ ቦምቦች ናቸው ፡፡

ስለዚህ ማንም የድብቅ ሸንጎ በመጥራት እኛ ላይ ብሎጋችንን ለማዘጋት ቢያሴሩ ፤ ከቤተክህነት በቀጥታ ለመንግስት ብሎጎቹ እንዲዘጉ ደብዳቤ ቢጻፍ ፤ መንግስትም ከራሱ ፍላጎት በመነሳት በሌላ አይን በመመልከት ብሎጋችንን ቢዘጋ ፤ እኛ ግን ከመጻፍ ወደ ኋላ የሚገታን አንዳች ነገር አይኖርም ፤ እነርሱ ለመዝጋት ካልደከማቸው እኛ አዲስ ለመክፈት አይሰለቸንም ፤ አፍራሽ ግብረ ሃይሎችን አይተን ዝም የምንልበት አይን ሰምተን ጆሮ ዳባ ልበስ ብለን የምናልፍበት ጆሮ የለንም ፤  ጽሁፎቻችን ዋልድባ ከሚገኙ መነኮሳት ጀምሮ በተለያዩ ሀገሮች ድረስ ተደራሽ መሆን ችሏል ፤ ቀድሞ በቀን ከ5ሺህ ሰዎች በላይ ቢጎበኙንም አሁን ብሎጉ ተዘግቶ ቢያንስ በቀን መረጃውን ከ3ሺህ በላይ ሰዎች ጋር ስለምናደርስ ተስፋ ባለመቁረጥ እንሰራለን፡፡

ቸር ሰንብቱ

Advertisements

“በጸሎታችሁ አስቡኝን ይመለከታል” የኢፌድሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ

በተጨማሪ ሁለት ገጾችን ኢትዮጵያ ውስጥ ለመነበብ እንሞክራለን

(አንድ አድርገን ሐምሌ 25 2004 ዓ.ም)፡- በቀደምት ዘመናት ኢትዮጵያን ሲያስተዳድሩ የነበሩ ነገስታት ሀገራቸው ላይ የተለያዩ ችግሮች በሚፈጠሩበት ጊዜ በየአህጉረ ስብከት ውስጥ የሚገኙ ገዳማት እና አድባራት “በጸሎታችሁ አስቡን” ፤ “በጸሎታችሁ አትርሱኝ” የሚል ደብዳቤ እንደሚጽፉ የታሪክ መዛግብት ይናገራሉ  ፡፡በጊዜው በቅርብም ሆነ በሩቅ ላሉ ገዳማትና አድባራትም “አትርሱኝ” እየተባለ ይነገራል ፤ ይጻፍላቸዋልም ይህንኑም አጥብቀው ለህዝቡ እና ለአባቶች  ማሳወቅ ጠቃሚ ስለሆነ በንጉሰ ነገስቱ ማህተም እየታተሙ ወደ ተለያዩ ገዳማት ይላካሉ ፤ በጊዜው ከተላኩት ደብዳቤዎች ለማስረጃ ያህል የሶስቱን ግልባጭ ከዚህ ቀጥለን ለማሳየት እንሞክራለን….

ጊዜው ድርቅ ሆኖ ለሰብል የሚያሰጋ በመሆኑ

 ዐዋጅ

ባለፈው ዘመን ሰብል መታጣት ስናዝን ይህው ዘንድሮም ጊዜው እንዳምናው ለመሆን የሚያሰጋ ሆኗልና አሁን ስለ ድርቁም ወደ እግዚአብሔር እንዘን፡፡ መስኖም እያወጣህ እህል ዝራ ፤ አታክልት ትከል ፤ ዳኝነትና ውርርድ ፤ ሰማኒያ ፤ የስድብ መቀጫ የገባውንም የተሰደበውንም ሰው ከሚካሰው ካሳ በቀር እስከ መጋቢት ሥላሴ ያለውን ምረናልና መኳንንቱም ሹማምንቱም ማርልን፡፡

መጋቢት 20 ቀን 1920 ዓ.ም መጋቢት 15 ቀን ተጻፈ

ሰንበትን በግዝት የተከለከለውን በዓል ስለማክበር

 
ዐዋጅ
በሰንበትና በግዝት በተከለከለው በዓል ቀን ሥራ እንዳይሰራ ተብሎ ከዚህ ቀደም ብዙ ጊዜ ዐዋጅ ተነግሮ ተከልክሎ ነበር ፤ አሁን ግን በተከበረው በዓል ቀን ይልቁንም ዕለተ ሰንበትን በመድፈርና ግዝትንም በመድፈር ፤ ግዝትም ዐዋጅም ጥሰህ ስራ እየሰራህ በዚህ ምክንያት በየጊዜው መቅሰፍቱ አልታገስ አለን፡፡ አሁንም ሰንበትንና ከዚህ ቀደም የተከለከለውን በዓል አክብር ፤ በተከለከለውም በዓል ቀን ስራ አትስራ ፤ በዚህ በግዝትና ባዋጅ በተከለከለው በዓል ቀን ሲሰራ የተገኝ ሰው ይቀጣል፡፡
ሀምሌ 16 ቀን 1920 ዓ.ም

ስለ ዘውድ በዓል አትርሱኝ

ሞአ አንበሳ ዘእምነገደ ይሁዳ
ቀዳማዊ ኃይለስላሴ
ሥዩመ እግዚአብሔር ንጉሰ ነገስት ዘኢትዮጵያ
ይድረስ፡-
እግዚአብሔር ከስጋ ከምወለዳቸው ከቃል ኪዳን እናቴ ወደ ኋላ አስቀርቶ የንጉሰ ነገስቱን ወራሽ ስላደረገኝ የዘውዱን በዓል ለማክበር አስቤ አለሁና በንጉሰ ነገስትነት በሚሰራ ስራ ሁሉ እሱ እግዚአብሔር  ሰሪ ሆኖ መሳሪያ እንዲያደርገኝ ከዛሬ ዠምራችሁ እስከ ዘውዱ በዓል ድረስ በጸሎት ምልጃችሁን ወደ እግዚአብሔር እንድታመላክቱኝ አትርሱኝ ብዬ እለምናችኋለሁ
1922 ዓ.ም ተጻፈ
ይህ ታሪክ የሚያሳየን እውነታ ቢኖር በዘመናት ይችን ሀገር እንደ አምላክ መልካም ፍቃድ ያስተዳደሯት ገዥዎቻችን ሀገር በእርዛት ፤ በርሀብ ፤ በዝናብ እጦት በችግር እና በጦርነት ስትወጠር በየአህጉረ ስብከቶች ያሉ ገዳማትና አድባራት ጋር “በጸሎታችሁ አትርሱኝ” የሚል ደብዳቤ እንደሚልኩ ማሳያ ነው ፤ ከዚህም በተጨማሪ እግዚአብሔር ምህረቱን እንዲያወርድላቸው ጸሎታቸውን እንዲሰማላቸው በእስር የሚገኙ ታራሚዎችን የመልቀቅ ልማድም ነበር ፤ ከታሪክ ጠቃሚውን ወስደን የማይጠቅመውን ብናስወገድ መልካም ይመስለናል ፤ አሁንም ሀገራችን ኢትዮጵያ በጠቅላይ ሚኒስትሯ ህመም የተነሳ ውጥረት ውስጥ ትገኛለች ፤ በዚህ ጊዜ መንግስት ይህን መልዕክት ለገዳም አባቶች ቢልክ ምን ይመስሎታል?

 

ጉዳዩ ፡- በጸሎታችሁ አስቡኝን ይመለከታል

 ለ፡- ዋልልድባ ገዳም ማህበረ መነኮሳት

 እንደሚታወቀው ላለፉት 21 ዓመታት ይችን ሀገር በጠቅላይ ሚኒስርነት መምራቴ ይታወቃል ፤ ከዚህ በፊት በማወቅም ሆነ ባለማወቅ ስላደረስኩባችሁ በደል አባቶቼ ሆይ ይቅር በሉኝ ፤ ሆኖም በአሁኑ ሰዓት በያዘኝ የጭንቅላት ህመም አልጋ ላይ ከጣለኝ ይህው ዛሬ 42ተኛ ቀኔን ቆጥሬአለሁ ፤ በዚች አጭር ጊዜ እግዚአብሔር ቸርና መሐሪ፥ ቍጣው የዘገየ፥ ምሕረቱም የበዛ አምላክ መሆኑን አውቄአለሁ ፤ እግዚአብሔር ምህረቱን እንዲልክልኝ በጸሎታችሁ እንድታስቡኝ ወደ እግዚአብሔር እንድታመለክቱልኝ አትርሱኝ ብዬ እለምናችኋለሁ፡፡
የኢፌድሪ ጠቅላይ ሚኒስትር
መለስ ዜናዊ..   
ሐምሌ 25 2004 ዓ.ም ተጻፈ
ቸር ሰንብቱ
ግብዓት፡- ከመጽሀፈ ዝክረ ነገር (ከብላቴ ጌታ ማህተመ ሥላሴ ወልደ መስቀል)

እረ ጉድ ነው

(አንድ አድርገን ሐምሌ 24 2004 ዓ.ም)፡- በአሁኑ ጊዜ የማይሰማ ነገር የለም ፤ በየቦታው የሚሰማው ነገር ጆሮን ጭው የሚያደርጉ ነገሮች እየሆኑ ለመስማትም ሆነ ለመጻፍ አስቸጋሪ ሁኔታ ላይ እንገኛለን ፤ የዛሬ 6 ወር ገደማ “እኔ እየሱስ ክርስቶስን የምወልደው ሴት ነኝ” ብላ የተነሳች ሴት መከሰቷን በጊዜው በቦታው ተገኝተን በአይናችን ካየነው ፤ በጆሯችን ከሰማነው ፤ ከጋዜጦች ካነበብነው እና ከፖሊስ መረጃ ጋር በማመሳከር አንድ ጽሁፍ ማቅረባችን ይታወሳል ፤ በጊዜው የተከሰተችው ሴት ከዚህ በፊት ተሰምቶም ሆነ ታይቶ የማይታወቅ ተግባር ስለፈጸመች ብዙዎችን ጉድ አሰኝታ ነበር ፤ ከሰማይ የወረደ  መና ነው በማለት ብዙዎችን ምንነቱ ያልታወቀ ምግብ አብልታቸዋለች ፤ ይህ ሁሉ ሲደረግ ስለ እሷ ሽንጣቸውን ገትረው የሚከራከሩ ብዙ ነጫጭ የለበሱ ሴቶችን አስከትላ ገድሏን ሲመሰክሩላት ሲመለከቱ ይህ ነገር ህልም እንጂ እውን አይመስሎትም ፤ እኛ ከተደረጉት ነገሮች ሁሉ ለእናንተው ጆሮ ለዘብ ያለውን ጉዳይ ብቻ አቅርበናል ፤ ይች ሴት የተነሳችበት ዓላማ በጣም አደገኛ ከመሆኑ የተነሳ ብዙዎችን “እኔ እግዚአብሔር የመረጠኝ ክርስቶስን የምወልደው ሴት ነኝ” በማለት በቤተክርስትያን ውስጥ በርካቶችን ያወዛገበች ፈት ሴት መሆኗን ለማወቅ ተችሏል ፤  በአዲስ አበባ አስኮ መንገድ የሚገኝው የአባታችን የአቡነ ሐብተማርያም ቤተክርስትያን በበአላቸው ቀን በመገኝት አውደ ምህረት ላይ በመውጣት ስትናገር የነበረው ነገር በርካታ ወጣቶችን በማስቆጣቱ ከፍተኛ ችግር መፈጠሩ የሚታወቅ ነው ፤ በጊዜው ያልተገባ ነገር ስትናገር የሰሙ ወጣት ምዕመናን ከአውደ ምህረት ላይ ውረጂ ሲሏት ባለመስማቷ አንጠልጥለው ሊያወርዷት ወደ አውደ ምህረቱ ሲያመሩ የሚመጣውን ጉዳት ከግምት በማስገባት ተሸቀንጥራ በግብር አበሮቿ አማካኝነት በመታጀብ  ቤተክርስቲያኑ ጎን  የሚገኝው መሰብሰቢያ አዳራሽ በመግባት ከተቆጡት ወጣቶች ማምለጥ ችላለች ፤  ይህ በእንዲህ እያለ በአዳራሽ ውስጥ አብረዋት የገቡት ግብር አበሮቿ ፖሊስ ዘንድ በመደወል ከሚደርስባት ጉዳት ሊያድኗት ችለዋል ፤ በጊዜው የነበሩ ወጣቶች ሁኔታውን ሲያስረዱ ስለ ቤተክርስቲያንና በድፍረት በአውደ ምህረት ላይ ስለተናገረችው ቃል እንባ እየተናነቃቸው ምግባሯንና ያደረገችውን ነገር መናገርና መግለጽ እስኪያቅታቸው ድረስ ደርሰው ነበር ፡፡

Read the rest of this entry

ፖሊስ በዋልድባ 49 መነኮሳትን ለማሰር እየፈለገ ይገኛል

 (አንድ አድርገን ፤ ሀምኔ 24 2004 ዓ.ም)፡- መንግስት አሁንም የዋልድባን መነኮሳት ማወከብ ማሰርና መደብደቡን አላቆመም ፤ ከዚህ በፊት በርካታ መነኮሳትና ወጣቶች መታሰራቸው በጊዜው ገልጸናል ከተለያዩ ድረ-ገጾች እና የዜና ማሰራጫዎችም ሰምተናል ፤ ከዚህ በፊት የታሰሩት መነኮሳት ስብእናቸውን በሚያዋርድ ሁኔታ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነትና ክብርን ዝቅ በሚያደርግ መልኩ እጅጉን አሸማቀው በክልሉ ፖሊስና በመከላከያ ሃይል አማካኝነት እያዳፉና በሰደፍ እየደለቁ ወስደዋቸው ፤ ከጥቂት ቀናት እስር በኋላም ደግመው ሊለቋው ችለዋል ፤ አሁን ግን መንግስት የያዘው አሰሳ በገዳሙ የሚገኙ ሁሉን አባቶችን የሚያሰጋ እየሆነ ይገኛል ፤ በገዳሙ የሚገኙትን መነኮሳት በጠቅላላ በሂደት ለመልቀም እንዲመቸው በመጀመሪያ ዙር 49 መነኮሳትን ማደን ተያይዞታል ፤ ከሚፈልጋቸው 49 መነኮሳት ውስጥ ሶስት ያህሉን ይዞ ወደ እስር ቤት አውርዷቸዋል ፤ ባሳለፍነው አርብ ከ3 እስከ 10 የሚደርሱ የመነኮሳትን ቤት ሲፈትሽ ውሏል ፤ ክፍት የሆኑት ቤቶች ላይ በቀጥታ በመግባት ፤ የተቆለፉትን ቤቶች ላይ ደግሞ ቁልፎቻቸውን ሰብሮ በመግባት ያለ ፍርድ ቤት ፍቃድ ቤቶቹን ሲበረብር ውሏል ፤ በጊዜውን “ከደጀ ሰላም” እና “ከአንድ አድርገን” ድረ-ገጾች ላይ ስለ ገዳሙ በተለያዩ ጊዜ የተጻፉ እና ፕሪንት የተደረጉ ጽሁፎች ፤ ስለዋልድባ ገዳም “ፍትህ” ጋዜጣ የዘገበችውን ዘገባ ጨምሮ ያስፈልጉኛል ያላቸውን ነገሮች ሁሉ አግበስብሶ ሊወስድ ችሏል ፤ በመሰረቱ የአንድ ሰው ቤት ወንጀለኛ ቢሆን እንኳን በህግ መሰረት መፈተሸ ያለበት ከፍርድ ቤት የወጣ ትእዛዝን መሰረት ተደርጎ ቢሆንም በማን አለብኝነት የተቀመጠው የሀገሪቱን ህግ የራሱ ጀሌዎችን በመላክ አፍርሶ ቤቶችን በጠራራ ጸሀይ ያለ ፍቃድ ሲያስበረብር ውሎ አምሽቷል ፤


 

 አሁንስ የት ሄደን አቤት እንበል ? አቡነ ጳውሎስ ቢመዘብሩት አላልቅ ያላቸውን ቤተክርስትያኒቱን ሃብት አንዴ ሸራተን አዲስ ሆቴል ፤ አንዴ ክራውን ሆቴል አንዴ ኢንተር ኮንቲነንታል እያሉ እንደጉድ እየዘሩት አሞራ ደግሰው እያበሉ ፤ የቁም ተስካራቸውን እያወጡ ይገኛሉ ፤ እርሳቸው ክብራቸውን ለመጨመር ሌት ተቀን ሲታትሩ ይታያሉ ፤ እርሳቸው በወንበሩ አይምጡባቸው እንጂ ስለ ዋልድባ ምን ጨንቋቸው ፤ ታዲያ በእምነታችን ውስጥ ቤተክህነቱ እና መንግስት ተባብረው በሚሰሩበት ሁኔታ ላይ እኛ የት ሄደን አቤት እንበል ? ድሮ ድሮ እንደ አባቶቻችን ስርዓት በእምነት ውስጥ የሚፈጠርን ችግር የበላይ ሆነው የመፍትሄ ሃሳብ የሚያፈልቁት ፓትርያርኮች ነበሩ ፤ አሁን ግን ይህን ሁኔታ በመቃወም ምእመናን የእዝ ሰንሰለቱን በመጠበቅ አቡነ ጳውሎስ ጋር ቢሄዱ ፌደራል ፖሊስ ጠርተው እንደሚያሳስሯቸው አሳልፈው እንደሚሰጧቸው እርግጠኞች ነን ፤ እና የት እንሂድ ?

 

ይህ በጅምላ የማፈስ አካሄድ አደገኛ ነው ፤ ትላንት ሶስቱን መነኮሳት አስሯል ፤ በቀጣይ ቀናት 46 መነኮሳትን ከያሉበት የመልቀም ስራውን ይሰራል ፤ እያለ እያለ የገዳሙን መነኮሳት በአታቸውን እስር ቤት የማድረግ ስራውን አጠናክሮ ይሰራል ፤ ይናገራሉ ይቃወማሉ የተባሉት ሰዎች በአንድም ይሁን በሌላ መንገድ ዳራቸውን የማጥፋት ስራ እየተሰራ ይገኛል ፤ ታዲያ እኝህን የመሰሉ መነኮሳት እጣቸው እስር ቤት ከሆነ ማንስ ሄዶ ስራቸው ይቃወማል ? ማንስ ስለ ገዳሙ ከፊት ይቆማል ?  በጣም የሚገርመው ነገር የትግራይ ተወላጅ የሆኑና መንግስትን የሚደግፉ በገዳሙ ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች ነገሩን ከሃይማኖት ጥያቄ አሳልፈው የብሔር ጥያቄ እያደረጉት ይገኛሉ ፤ እነዚህ አካላት የዋልድባል ልማት የሚቃወሙ አባቶችን “ ትግራይ እንዳትለማ የሚፈልጉ ሰዎች ናቸው” በማለት የገዳሙ መነኮሳትን ለፖሊስ እየጠቆሙ ይገኛሉ ፤ እነዚህ ጥቂት ሰዎች እና መነኮሳት አብረው ስብሰባ በመግባት ስብሰባው ሳይበተን የተያዘውን አጀንዳ ፤ ተነጋገሩበት ጭብጦች ፤ የተወሰደውን አቋም ሳይቀር በደቂቃዎች ውስጥ በሞባይል አማካኝነት ለመንግስት ባለስልጣናት ለክልሉ የፖሊስ አዛዦች ጭምር ያደርሳሉ ተብሏል ፤ ይህን ምን ይሉታል ?  “ጠላቴን እኔ እጠብቀዋለለሁ ወዳጄን አንተው ጠብቅልኝ” የሚያስብል ዘመን የመጣ ይመስላል ፤ ለዛውም ዋልድባ…..

 

እረ እባካችሁ በእግዚአብሔር እጅ የተያዘች ነፍስ እያለች ግፍና በደላችሁን አታብዙት ፤ “በማንም ግፍ አትሥሩ” ሉቃስ 3፤14 እግዚአብሔር ዝም የሚለው አላማ ስላለው ነው ፤ መጽሀፈ መክብብ 3፤7 ላይ “ዝም ለማለት ጊዜ አለው፥ ለመናገርም ጊዜ አለው” ይላል አሁን ጊዜው የእግዚአብሔር የዝምታ ጊዜ ሊሆን ይችላል ፤ የሚናገርበት እጁን የሚያነሳበት ኃይሉን የሚያሳይበት ጊዜም እንዳለው አትርሱ ፤  “እኔንም ስማ ዝም በል፥ እኔም እናገራለሁ።” መጽሀፈ እዮብ 33፤31 እግዚአብሔር ጊዜው ሲደርስ እንደሚናገር እናምናለን ፡፡ እኛ ግን ዘወትር ”አቤቱ፥ ዝም አትበል፥ ቸልም አትበል።” መዝሙረ ዳዊት 83፤1 እያልን ስለ ገዳማችን በእንባ እንጸልያለን፡፡

 

ፈርኦን ልቡ አብጦ ተው ሲባል አልሰማ ብሎ እስራኤላውያንን ከኋላቸው በፈረስ ሊያጠፋቸው ሲከታተላቸው ባህሩን የከፈተ እግዚአብሔር ሰራዊቱ ጠቅልሎ እስኪገባ ድረስ ዝም አለ ፤ የፈርኦርን ሰራዊትም በፍጥነት ለእስራኤላውያን በተከፈተው ባህረ ኤርትራ ላይ ጠቅልለው ገቡ ፤ የእስራኤል እግር ከባህሩ ሲለቅ የፈርኦን ሰራዊት እግር ጠቅሎ ሲገባ የተመለከተ ሁኔታዎችን ሁሉ ዝም ያለ እግዚአብሔር የተከፈተውን ባህል በላያቸው ላይ ከደነባቸው ሁሉም በባህር አለቁ ፤ የእግዚአብሔር ዝምታ ጊዜ የሚጠብቅ መሆኑን እወቁ አሁንም እኮ አምላካችን እያስተማራችሁ ይገኛል ፤ የሚማር ልቦና ባይኖራችሁም ፤ ላይቀጣችሁ እየራራላችሁ ከስህተታችሁ እንድትመለሱ በመፈለግ ዝም ብሏችሁ ይገኛል ፤ የማንንም ውድቀት የማይፈልግ አምላክ የተሰጣችሁን እድል ካልተጠቀማችሁበት እንደ ፈርኦር ሰራዊት ባህሩን እንዳይከድንባችሁ ተጠንቀቁ ፤ እኛ እርግጠኛ ሆነን መናገር የምንችለው በዋልድባ ላይ ግድብ ተሰርቶ ሰላም እንደማትሆኑ ብቻ ነው ፤ እግዚአብሔር ቀን አለው……….

 

ስለ ዋልድባ በመጪው ሱባኤ በርትተን እንጸልይ

 

 

 

ለዋልድባ ቤተ ሚናስና ለቤተ ጣዕመ ክርስቶስ ማህበረ መነኮሳት የተጻፈ ደብዳቤ

 

(አንድ አድርገን ሐምሌ 23 ቀን 2004 ዓ.ም)፡- የዛሬ 102 ዓመት ወደ ኋላ ሄደን ታሪካችንን ስንቃኝ በጊዜው ዋልድባ ገዳም ቤተ ሚናስና ለቤተ ጣዕመ ክርስቶስ ማህበረ መነኮሳት መካከል በተነሳው የኃይማኖት ችግር በገዳሙ ውስጥ ያሉትን አባቶች ለብዙ ጊዜ ካከራከራቸው በኋላ ከማዕከላዊ መንግስት አፄ ምኒሊክ ዘንድ ጉዳዩ ደርሶ ምን ዓይነት መልስ እንደጻፉላቸው ለእናንተው አስተማሪ ሆኖ ስላገኝነው ለማቅረብ ወደድን፡፡

ቅድመ ታሪክ

አባ ጣዕመ ክርስቶስ ወደ ዋልድባ ገዳም ሲገቡ  ከውጭ መንኩሰው ነበር ፤ ስምረትን ግን የተቀበሉት ዋልድባ ገባም ውስጥ ማይፈዴ በተለይ አይጠየፍ ከተባለው ቦታ መሆኑን መዛግብት ያስረዳሉ ፤ ስምረትንም ያነሱአቸው አባት ናኩቶ ለአብ የመንፈስ ቅዱስ ልጃቸው የሆኑት አባ ገብረሚካኤል ናቸው ፤ እኒህ ሰው የሚታመሙትን መነኮሳት ሁሉ ሳይሰቀቁና ሳይጠየፉ ሁሉን አቅፈው ደግፈው ስለሚያስታምሙ አይጠየፍ የሚል ቅጽል ስም ተሰቷቸዋል ፤ ስለዚህ አብዛኛውን ጊዜ አባ ገብረሚካኤል በማለት ፋንታ አባ አይጠየፍ እየተባሉ ይጠሩ ነበር ፤ ይህን በጎ ተግባር ሲፈጽሙበት የነበረውም ቦታ በርሳቸው ስም አይጠየፍ እየተባለ እስከአሁን ይጠራል፡፡

አቡነ ጣዕመ ክርስቶስ ወደ ዋልድባ ገዳም የገቡት  በ1823 ዓ.ም ነበር ፤ አባ ጣዕመ ክርስቶስ ከቤተ እስጢፋኖስ ቤት ገብተው ጥቂት ዘመን እንደቆዩ ለእስጢፋኖስ ቤት አበምኔት ሆኑ ፤ ወዲያው የአባ እስጢፋኖስ ስም ተዘርዞ የአባ ጣዕመ ክርስቶስ ስም ተተክቶ ቤተ ጣዕመ ክርስቶስ ተብሎ ተሰየመ፡፡ ነገር ግን የአቡነ እስጢፋኖስ ስም ተሰርዞ የአባ ጣዕመ ክርስቶስ ስም ቢተካም ፊት እንደቆየው ስርዓት በሊቀ አበምኔቱ ሥልጣን ስር ሆነው በሰላምና በፍቅር ቆዩ እንጂ ከሊቀ አበምኔቱ ስልጣን ስር ወጥቼ እራሴን ችዬ እኖራለሁ ሲሉ ያቀረቡት ሃሳብ  አልነበረም፡፡

አባ ጣዕመ ክርስቶስ ካረፉ በኋላ ፤ ሲያስተዳድሩት የነበረው ማህበር እየተዳከመ እና እየተመናመነ ስለሄደና የቀሩትንም ጥቂቶቹ መነኮሳት በዋሻ የነበረውን ችግርና ፈተና ሊቋቋሙት ባለመቻላቸውና ክፉ ዘመን ስለገባ መጻህፍቶቻቸውን  ትተው ቀርተው የነበሩ 5  መነኮሳት በሙሉ ከገዳሙ ወጥተው ሄዱ፡፡ በዚህ ጊዜ ሊቀ አበምኔት የነበሩት ገብረ ክርስቶስ የሚናስ ልጅ ጌታዬ መምህር ማኅጸንተ ጊዮርጊስ ደወል ደውለው ማህበሩን ከውነው የአቡነ እስጢፋኖስን መጻህፍት ሰብስበው ምልክት አድርገው ወደ እቃ ግምጃ ቤት እንዲቀመጥና ወደ ፊት የእስጢፋኖስ ልጆች በመጡ ጊዜ አትከልክሏቸው ስጧቸው ብለው ለመነኮሳቱ ተናገሩ ፤ ከተሰደዱት ከ5  መነኮሳት የችግር ጊዜው ካለፈ በኋላ ሁለቱ በ1886 ዓ.ም ተመልሰው መጥተው ከገዳሙ ገብተው በቆየው ስርዓት መሰረት ለመቀመጥ ማህበሩን ጠየቁ ፤ በዚህ ጊዜ መከራውን ታግሰው ፤ ታቦታቸውንና መጻህፍቶቻቸውን ጠብቀው ማህበሩ እንዳይፈታ ተንከባክበው ከውነው የቆዩት ገብረ ክርስቶስ የሚናስ ልጆች ከእኛ ጋር ተቀላቅላችሁ ልትኖሩ ሌላ ደውል ላትተክሉ አበምኔትም ላትሾሙ በዚህ ቃል ግቡና ተቀመጡ አሏቸው፡፡  እነርሱም ለጊዜው ከዚህ የተሻለ አማራጭ መንገድ ስላልነበራቸው በዚህ ውል ተስማምተው ስምምነቱንም በጽሁፍ ተጻጽፈው ከማህበሩ ተቀላቀሉ ፡፡ ከማህሩ ተቀላቅለው ለ7 ዓመት አብረው ከኖሩ በኋላ በ1893 ዓ.ም ከዋሻ ተነስተው ወደ ጥንት ቦታቸው አሁን ወዳሉበት ወረዱ ፤ በዚያ ጊዜ  የአቡነ ጣዕመ ክርስቶስ ልጆች መበርከት ጀመሩ ፤ ይህን ሁኔታ እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም “ራሳችንን ችለን ደውል እንተክላለን ፤ አበምኔትም አንሾማለን” ሲሉ ክርክር አበቀሉ ፤ የቤተ ሚናስ ቤቶችም “የለም ቃላችሁን ልታፈርሱ መሃላችሁን ልትጥሱ አይገባም ፤ ከእኛ መለየት የለባችሁም” ሲሉ ተከራከሩ ፡፡ ነገሩ ከዚያው ከቤታቸው መፍትሄ ሊያገኝ ባለመቻሉ ተያይዘው ወደ አጼ ምኒልክ ዘንድ አዲስ አበባ በ1900 ዓ.ም ሄዱ ፤ ሁለቱም ወገኖች ከእቴጌ ጣይቱ ብጡል ቀርበው ነገራቸውን አስረዱ ፤ እቴጌም ለማስማማት ብዙ ጥረት አደረጉ ፤ ነገር ግን የሁለቱ ማኅበራት ተወካዮች ሊስማሙ ባለመቻላቸው “ወደፊት አንድ መፍትሄ እስኪደረግለት ድረስ እንደ ጥንቱ ሁናችሁ ቆዩ” ብለው አሰናበቷው ፡፡ ስለሆነም እቴጌ “እንደ ጥንቱ” ሲሉ ደውላችሁን ተክላችሁ ፤ አበምኔታችሁን መርጣችሁ ፤ በሊቀ አበምኔታችሁ ስር ሆናችሁ ቆዩ ማለታቸው ነበር እንጂ አንደኛውን ለይታችሁ ተቀመጡ ማለታቸው አልነበረም፡፡ ስለሆነም ይህን ምክንያት በማድረግ ቤተ ሚናስና ቤተ ጣዕመ ክርስቶስ ፈጽመው ተለያዩ ፤ ከላይ እስጢፋኖስ ዝቅ ሲል የጣዕመ ክርስቶስ ልጆች የሆኑት የጣዕመ ክርስቶስ ቤት ብለው ክፍል ለዩ ፤ ከኛ መለየት አይገባችሁም ብለው ሲከራከሩ የነበሩት ከላይ የገብረ ክርስቶስ ዝቅ ሲል የሚናስ ልጆች የሆኑት ቤተ ሚናስ ብለው ክፍል ለዩ ፤ ይህ ሁሉ የሆነው በ1900ዓ.ም ነበር ፡፡

ይህ ከሆነ ከጥቂት ጊዜ በኋላ “መሬቱንም ውሃውንም አካፍሉን የአባታችንን የእስጢፋኖስን መጻህፍቶች አስረክቡን” ብለው ጠየቁ ፤ የቤተሚናስ ማህበርም ጠብቀው ያቆዩትን መጻህፍት የእስጢፋኖስ ድረሻ የሆነውን አስረከቡ ፤ እንዲሁም መሬቱንና ውሃውንም ከፍለው ሰጡ ፤ በዚህ ገዳም ውስጥ ከአቡነ ሳሙኤል ቀጥለው በጣም ጎልተው የሚታወቁት አቡነ ሚናስ ናቸው፡፡ አቡነ ሚናስ የማህበሩ መብራትና ምሰሶ የፍቅር የአንድነት ሃይማኖት ምንጭ የነበሩ ትልቅና ቅዱስ የሆኑ አባት ናቸው፡፡ ከተለያዩም ወዲህ ቤተ ሚናስ ለብቻቸው አንድ መምህር መሾም ጀመሩ እንዲህም ከተደረገ በኋላ ለጠቡና ለክርክሩ መነሻ የሆነውን የአትክልት ቦታ እንዲሁም በገጠር ያለውን ርስት ጉልት ተከፋፈሉ ፡፡ ሌላ ቤተክርስትያን እንዳይተከል ተደርጎ ጥንት አባቶቻቸው  በአንድ ላይ ሁነው ሲጸልዩባት  የነበረችው የአቡነ ገብረክርስቶስ ታቦት በታቦተ ኪዳነምህረት ብቻ እንዲጸልዩ ተስማሙ ፤ በዚህ ዓይነት ነገሩ አልቆ ለጥቂት ጊዜ ሰላም ተፈጥሮ እንደኖሩ በአትክልቱ እና በጉልቱ ሲያጣላቸው የነበረው ሰይጣን ነገሩን ወደ ኃይማኖት አዞረና በኃይማኖት ምክንያት(በሚስጥረ ስላሴ) ጥል ተጀመረ፡፡ በፊት በርስቱ ሲጣሉ የነበሩ ሁለቱ ማህበራት ችግራቸው አልፎ አልፎ ካሆነ በቀር ወደ ውጭ አይወጣም ነበር ፤ በዚያን ወቅትም ብዙዎች መነኮሳት አይተባበሩም ነበር፡፡ በኃይማኖት ምክንያት በተነሳው ጠብና ክርክር ግን ሁሉም ተባበሩ ፤ ብዙ ትሩፋትና ተዓምራት በተሰራባት ቦታ ሁከትና ጸብ ጸናባት ፤ መካነ ፈላስያን መካነ ግሁሳን ገዳማት የተባለችው ቦታ የሁከት ቦታ ከመባል ደረሰች ፤ በኃይማኖት ምክንያት በተነሳው ጥል  ከገዳማቸው ተነጋግረው መፍትሄ ሊሰጡት ባለመቻላቸው ጠቡና ክርክሩ እየባሰ ሄዶ አጼ ምኒልክ ዘንድ አደረሳቸው፡፡ አጼ ምኒልክም በጊዜው በነበሩ ሊቃውንት አማካኝነት ይህን ደብዳቤ ላኩላቸው፡፡

ሞአ አንበሳ ዘእምነገደ ይሁዳ ዳግማዊ ምኒልክ ሥዩመ እግዚአብሔር ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ

በሃይማኖት ነገር አንድ መለኮት ሶስት መለኮት በማለት እርስ በርሳችሁ ስለተጣላችሁበት አባቶቻችን ሐዋርያት ×ç ሊቃውንት ከጻፉት መጻህፍት አዋጥተን እንጽፍላችኋለን ቃሉም ይህ ነው፡፡

ወላጅ መለኮት(አብ) ተወላጅ መለኰት(ወልድ) ሠራጺ መለኮት በአካል ሦስት በግብር ሦስት በስም ሦስት ነው ፤ በመለኰት በባሕርይ በፈቃድ አንድ ነው ፤ እንጂ × መለኰት ብሎ በአኃዝ አይነገርም፡፡

ምስክር አግናጥዮስ የጳጳሳት አለቃ በአንጾኪያ እንዲህ ብሏል ፤ “ይህች ሦስትነት ያለመለየት ያለመለወጥ በሦስት አካላት በአንድ መለኰት የተካከለች ናት እነዚህን ሦስቱ አካላት በጌትነት በክብር ፍጹማን ናቸው በአንድ መለኮት አንድነትም አንድ ናቸው፡፡ ይኽውም ሦስትነት ከእርሱ የሚገኝ አንድ ብርሃን ነው በዓለም ሁሉ ሙሉ ነው፡፡”

አትናቴዎስ ፤ ሐዋርያውም የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት “አብ አምላክ ነው ወልድም አምላክ ነው ፤ መንፈስ ቅዱስም አምላክ ነው ፤ ግን ሦስት አማልክት አይባሉም ፤ አንድ አምላክ ነው እንጂ ሁለተኛም የሦስቱ አካላት መለኰት እንደሆነ ቅዱሳት መጽሐፍት ያስረዳሉ እነዚህም አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ ናቸው ፤ መለኮት አንድ ነውና የአብ የወልድ የመንፈስ ቅዱስ የባሕርይ አንድነታቸው ነው ፤ የሦስቱ አካላት መለኰት አንድ እንደሆነ በዚህ አወቅን፡፡ እነርሱም በመለኮት ከአብ ጋር አንድ ነውና መለኮት የማይከፈል አንድ ሲሆን ሥላሴ በሦስት አካል ፍጹም ነው፡፡ በሦስቱ አካላት ስም እንደማያምኑ እንደተረገሙ እንደ ፎጢኖስ እንደ መርቅሎስ ሦስቱን አካላት አርዮስም እንደካደ የሦስቱን አካላት አንድ መለኮት አንክድም አናቃልልም” ብሏል፡፡

ባስልዮስ የቂሳርያ ኤጲስ ቆጶስ “የሶስቱ አካላት መለኮት ፍጹም አንድነትን ልናውቅ ይገባል ፤ የእነርሱ የሚሆን አንድ መለኮትን አንድ በማድረግ እናዋህድ በአብ ወላዲነት አስራጺነት መለኮት አንድ አንደሆነ ኃይማኖትን እንመን ፡፡ ወልድ ከአብ ተወልዶአልና መንፈስ ቅዱስም ከአብ ተገኝቷልና አብ ከወልድ ወልድም ከመንፈስ ቅዱስ ሳይቀድም ፤ ወልድ ከአብ በመወለዱ መንፈስ ቅዱስም ከአብ በመስረጹ የፈጣሪያችን የሦስትነቱ መለኮት አንድ ይሆናል” ብሏል፡፡

ቄርሎስም የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳስ “አብ በአካሉ ፍጹም አንድ ነው ፤ ወልድም በአካሉ ፍጹም አንድ ነው ፤ መንፈስ ቅዱስ በአካሉ ፍጹም አንድ ነው ፤ እነዚህ ሦስቱ እንደ መንግስት ማዕረግ አይደሉም ባሕርያቸው አንድ አገዛዛቸው አንድ ነው እንጂ” ብሏል፡፡

ዮሐንስም የኢየሩሳሌም ኤጲስ ቆጶስ እኒህ ሦስቱ አካላት በመልክዕ ፍጹም ሆነው በመለኮት አንድ እንደሆኑ እናምናለን ብሏል ፡፡ ጎርጎርዮስም ዘእንዚናዙ ስለ ሦስት አካላት ትክክልነት ስለማይከፈል ስለ መለኮት አንድነቱ እንዲህ አለ ፤ “ከሁሉ አስቀድሞ በአካል ልዩ በክብር አንድ የሚሆን ሦስትነትን እናስተምራለን እነዚህም አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ ናቸው፡፡”

ሥላሴ በመለኮት አንድነት መለየት የለባቸውም ፤ አካላት ግን በባሕርይ መለየት ሳይኖር እየአንዳንዱ አካል በገጽ በመልክ ፍጹም ነው ብሏል፡፡ ዮሐንስም የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት “እኛስ ወልድን ከአብ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር በመለኮት አንድ እንደሆነ እናምናለን” አለ ፡፡ የሦስቱ አካላት መለኮት አንድ እደሆነ የማያምን ሰው ቢኖር እኛ እናወግዘዋለን ብሏል፡፡

ብንያም ፤ የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት በአካል ሦስት በባሕርይ አንድ የሚሆኑ በተመሰገኑ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ እናምናለን እንበል ሦስት አካላት በስራው ሁሉ በማድረግ ፤ በመናገር በመለኮት አንድ ናቸው ብሏል፡፡

ባስልዮስም የአንፆኪያ ሊቀ ጳጳሳት እነርሱ መለኰት ባሕርይ እንደሆኑ በእነርሱ አምናለሁ እታመናለሁ ልዩ ልዩ የሚሆኑ አካላት ከመለኰታዊ ባሕርይ ልዩ ናቸው አልልም መለኮትስ አካላት ነው ፤ እነዚህ ልዩ የሚሆኑ ገጻት ናቸው፡፡

አባ መቃርስም የእስክንድርያው ሊ ጳጳስት  እኛ የሦስቱ አካላት ባህርይ አንድ እንደሆነ የሦስቱ አካላት ባሕርይም መለየት እደሌለበት እናውቃለን መለኮት ሦስቱን አካላት አንድ እንደሚያደርግ የታወቀ ነው ብሏል፡፡ ዮሐንስም የእስክንድርያው ሊቀ ጳጳሳት በአካል ሦስት በመለኮት አንድ ናቸው ፤ አንድነትን ሶስትነትን የተናገረ ጎርጎርዮስ የሦስቱ አንድ ነው ሦስቱም በመለኮት አንድ ናቸው ብሎ ተናግሯል፡፡

ሁለተኛም ከቴዎዶስዮስ እኛስ ብዙ አማልክትን የሚያምኑ በባህርይ መለኮቱ በማይከፈል በአንድ እግዚአብሔር ልዩ ባሕርያትን የሚናገሩ የመናፍቃን ነገር እንነቅፋለን ደግመኛም የአብ የወልድ የመንፈስ ቅዱስ መለኮት ሦስት ነው የሚሉት እናወግዛለን ብሏል ፡፡

ዮሐንስም የአንጾኪያ ሊቀ ጳጳስ አብ ሕይወት ነው ወልድ ህይወት ነው ፡፡ መንፈስ ቅዱስም ሕይወት ነው ፤ ዳግመኛ አብ አንድ ይባላል ወልድም አንድ ይባላል ፤ መንፈስ ቅዱስም አንድ ይባላል ከአካላት አንዱም አንዱ በባህርይ አንድ ናቸው ፤ አንድ አምላክ ናቸው ፤ ግን ሶስት አማልክት አይባሉም ማመናችንም እንደ ሦስት ሰዎች ሦስት አማልክት ብለን በሦስት መለኮት አይደለም ፤ ልዩ በሆኑ በሦስቱ አካላት በሦስቱ ገጻት አንድ ባሕርይ አንድ መለኮት ገንዘብ በሚሆኑ ገጻት በስም በግብር ሦስት ናቸው ብለን እናምናለን እናሳምናለን ብሏል፡፡

እንግዲህ በዚህ ጸንቶ መኖር ነው ፤ ከዚህ ቃል የወጣ ሰው ቢገኝ በሥጋው መንግስት ይቀጣዋል በነፍሱም አባታችን አቡነ ማቴዎስ አውግዘዋል፡፡

በግንቦት በ24 ቀን 1902 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ ተጻፈ፡፡                 

ቸር ሰንብቱ

ግብአት ፡- የዋልድባ ገዳም ታሪክ (ከበሪሁን ከበደ)

 

Egyptian Coptic activists declare creation of Christian Brotherhood

“ሙስሊም ወንድማማቾች የፖለቲካ ፓርቲ” ለመመስረት ጥያቄ መቅረቡ ተሰማ

የተሃድሶያውያኑ ቀበሮ መነኩሴ

አሁንም ቤተክህነቱ ዋልድባ አልተነካም ይላል

“ማኔ ቴቄል ፋሬስ” ብሎ የሚጽፈው ጣት እንዳይቀርብባችሁ ለራሳችሁ ተጠንቀቁ