በባቦጋያ ምስራቀ ፀሐይ ቤተክርስቲያን ለጠፈጠረዉ ዉዝግብ በፍትሐብሔር ሕግና በቃለዓዋዲዉ አኳያ ሲታይ

የአባቶቼን ርስት እሰጥህ ዘንድ እግዚአብሔር ያርቅልኝ (1ነገ20፡11)

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
በባቦጋያ ምስራቀ ፀሐይ ቤተ ክርስቲን ለጠፈጠረዉ ዉዝግብ መነሻ የሆነ በደብሩ የሰበካ ጉባኤ ተወካዮችና በአቶ ታዲዎስ ጌታቸዉ መካከል የተፈረመዉ ዉል በፍትሐብሔር ሕግና በሕገመንግስቱ እንዲሁም በቃለ ዓዋዲዉ ሲታይ

1.1 በፍትሐብሔር ሕግና ሕገ መንግስት ዉሉ ሲተነተን
የባቦጋያ ምስራቃ ፀሐይ መድሃኒአለም ቤተ ክርስቲያን ሰበካ ጉባኤ ሰኔ 2/1999ዓ.ምያሳለፈዉን ዉሳኔ መሰረት ማድረግ ሰኔ 10/2004ዓ.ም በበጎ ፈቃደኝነት የተደረገ የዉል ስምምነት በሚል ርእሰ የኩሪፍቱ ሪዞርትና ስፖ ባለቤት ከሆኑት ከአቶ ታዲዎስ ጌታቸዉ ጋር ባደረጉት የመንደር ዉል የቤተ ክርስትያንቱን የመስቀልና የጥምቀት በዓላት ማክበሪያ የነበረዉን 13,020 ካሬ ሜትር ስፋት ያለዉን ፤ በስተ ደቡብ ከኩሪፍቱ ሐይቅ ጋር የሚዋሰነዉን ቦታ እንድታጣ አድርጓታል፡፡ይኼ በወቅቱ የደብሩ ሰበካ ጉባኤ አስተዳደርና በአቶ ታዲዎስ ጌታቸዉ መካከል የተደረገዉ ስምምነት ከኢትዮጵያ የፍትሐብሔርና ሕገመንግስት ሕግ ማእቀፍ ዉጭ የሆነ፣የስምምነቱ ርእሰ ጉዳይ ወይም የዉለታዉ ጉዳይ (object of the contract) ተለይቶ የማይታወቅ እና ይልቁንም በዉስጡ የተገለፀዉን ለአቶ ታዲዎስ የቤተ ክርስቲያንቱን መሬት በነጻ የመስጠትን ዓላማ ማረጋገጥ የማይቻል ሲሆን በአንፃሩ ቤተ ክርስቲያንቱ ሐይማኖታዊና ብሔራዊ በዓላቶቿን የምታከብርባቸዉን ቦታዎች ያለ አንዳች ጥቅም እንድታጣ ያደረገ እና የቢሾፍቱ ከተማን ማዘጋጀ ቤት በማወቅም ሆነ ባለማወቅ በቸልተኝነትም ይሁን ሆን ተብሎ ሕገ-ወጥ እና ኢ-ፍትሐዊ የሆነና የሚያስወቅስ ድርጊት እንዲፈፅም ምክንያት የሆነ ስምምነት ነዉ፡፡

በመሰረቱ ዉል ማለት ሁለት ወይም ከዚያ በላይ የሆኑ ሰዎች ንብረታቸዉን የሚመለከቱ ግዴታዎችን ለማቋቋም ወይም ለመለወጥ ወይም ለማስቀረት ባላቸዉ ተወዳዳሪ ግንኙነት የሚደረግ ስምምነት ማለት እንደሆነ የኢትዮጵያ የፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 1675 ያስረዳል፡፡ስለሆነም ዉል ማለት ለፍሰቱም ሆነ ለአፈፃፀሙ የሕግ ዋስትና ያለዉ እና በተዋዋይ ወገኖች ላይ የአሳሪነት እና የአስገዳጅነት ዉጤት (binding effect) ያለዉ ስምምነት ነዉ፡፡ይሁን እንጂ የፍትሐ ብሔር ሕጉ ማንኛዉንም አይነት ስምምነት ዉል በማለት አይጠራም እንዲሁም የሕጋዊነት እዉቅና አይሰጥም፡፡ስለሆነም አንድ ስምምነት ዉል ለመባልና ሕጋዊ ዉጤት ይኖረዉ ዘንድ አራት ቅድመ ሁኔታዎች (elements) ተሟልተዉ መኖር አለባቸዉ፡፡

1ኛ የተዋዋይ ወገኖች ችሎታ (capacity)፣

2ኛ የተዋዋይ ወገኖች ፈቃድ/ይሁንታ (consent)፣

3ኛ የዉለታዉ ጉዳይ (object) እና

4ኛ የዉሉ የአፃፃፍ ፎርም (formality) ናቸዉ፡፡

ከእነዚህ 4ኛዉ ሕግ በግልፅ የሚያስገድድ ካልሆነ በስተቀር እንደ ተዋዋይ ወገኖች ምርት አለባቸዉ፡፡ከዚህ አንጻር ከላይ የተጠቀሰዉ የደብሩ ሰበካ ጉባኤ እና በአቶ ታዲዎስ ጌታቸዉ መካከል የተደረሰዉ ስምምነት ባሕሪይና ሕጋዊነት ምን እንደሚመስል ለማየት እንሞክር፡፡

በመጀመሪያ በዚህ በተጠቀሰዉ ስምምነት ዉስጥ የሰፈረዉን የቤተ ክርስቲያንቱን ቦታ ለባለሃብቱ አሳልፎ የመስጠት ጉዳይ ተስማሚዎቹ ማለትም የደብሩ ሰበካ ጉባኤ ተወካዮቹና ባለሃብቱ አቶ ታዴዎስ በሙሉ ፍላጎት ፈቅደዉ እና አስበዉ ያደረጉት በመሆኑ ፈቃድ የሚለዉ ቅድመ ሁኔታ ተሟልቷል፡፡በመቀጠልም ሁለቱም ተስማሚ ወገኖች ሕጋዊያን ተግባራትን(Juridical acts) ለመፈጸም ችሎታ ያላቸዉ በመሆኑ ይኸም እንደ ቅድመ ሁኔታ ተሟልቷል ማለት ይቻላል፡፡ በ3ኛ ደረጃ ግን የዉለታዉ ጉዳይ አስመልክቶ የፍትሐ ብሔር ሕጉ አንቀፅ 1714(1) ተዋዋይ ወገኖች የሚዋዋሉበትን ጉዳይ በትክክል እና በግልፅ ለይተዉ ማስቀመጥ አለባቸዉ ሲል ይደነግጋል፡፡ይሁን እንጅ የደብሩ ሰበካ ጉባኤ እና የባለሃብቱ ስምምነት ከርዕሱ ጀምሮ ይዘቱ ሁሉ ግልፅነት የጎደለዉ እና በደፈናዉ የተፃፈ ለአፈፃፀሙም ምንም አይነት ዋስትና እና ተጨባጭነት የሌለዉ ነዉ፡፡  ሲጀምር ርዕሱ ‹‹በበጎ ፈቃደኝነት የተደረገ የዉል ስምምነት›› በሚል የተፃፈ ሲሆን ይኸም ስምምነቱ የቦታ ኪራይ ፤ ወይም የቦታ ስጦታ ወይም የቤት ወይም የሌላ ንብረት ሽያጭ ወይም ሌላ የዉል አይነት እንደሆነ በፍፁም ግልፅ አይደለም፡፡በተጨማሪም በስምምነቱ ፅሑፍ ይዘት ዉስጥም የሠፈሩት ሐሳቦች ባለሃብቱን አቶ ታዲዎስን ያለምንም ቅድመ ሁኔታ በነፃ ለመጥቀምና በአንፃሩ የቤተ ክርስቲያንቱን መብት ለመጉዳት እና ጥቅሟን ለማሳጣት ታስበዉ በተዘጋጀ ቃላት እና አገላለፆች የተሞሉ ከመሆናቸዉ በስተቀር በሕግ እዉቅና ያለዉ እና ግልፅ የሆነ የዉለታ ጉዳይ አያፀባርቅም፡፡

የአንድ ሕጋዊ ዉል የዉለታ ጉዳይ የተዋዋይ ወገኖችን መብትና ግዴታ በቂ እና ግልፅ በሆነ መልኩ ማስቀመጥ ሲሆን የእነ ታዲዎስ ዉል ግን ከዚህ በእጅጉ የራቀ ነዉ፡፡ ለዚህ ማሳያ የሚሆነን በስምምነቱ 3ኛ አንቀጽ ዉስጥ ዉል ተቀባዩ እና መሬት ተቀባዩ አቶ ታዲዎስ ጌታቸዉ በቦታዉ ላይ ግንባታ አጠናቀዉና በይፋ ሥራ ጀምረዉ ጥቅም ማግኘት በጀመሩ ከመጀመሪያዉ ወር ጀምሮ በየወሩ 20000(ሃያ ሺህ ብር) በግል ፈቃደኝነትና በበጎ አድራጎት ስም ለቤተ ክርስቲያንቱ ሰበካ ጉባኤ ገቢ ያደርጋሉ የሚል ሐሳብ ሰፍሯል፡፡

እንግዲህ የዉል ተቀባዩ የመሬት ወሳጁ የአቶ ታዲዎስ ግዴታ ተብሎ የተቀመጠዉ ብቸኛዉ ጉዳይ ግንባታ አካሂደዉ ገቢ ማግኘት ከጀመሩ በኋላ የተባለዉን 20000 ብር መክፈል ነዉ፡፡ ይኼ ግን በግል ፈቃደኝነታቸዉ ሲሆን ክፍያዉም ገቢ የሚደረገዉ በበጎ አድራጎት ስም ነዉ፡፡ታዲያ እኒህ ሰዉ መሬቱን የራሳቸዉ ካደረጉ በኋላ ግንባታም ከጨረሱ በኋላ በምን ግዴታ እና በየትኛዉ የዉል ማዕቀፍ የተባለዉን ብር ይከፍላሉ? ነዉ ወይስ በእኝህ ሰዉ ላይ ምን አይነት የዉል ግዴታ ለመፍጠር ተፈልጎ ነዉ? ቤተ ክርስቲኒቱስ እንዴትና በምን እንድትጠቀም ታስቦ ነዉ? ይልቁንም ቤተ ክርስቲያኒቱን የሚጎዳ አገላለፅ ያለዉ እና የሕግ ሽፋን እና ዋስትና የሌለዉ ተራ ስምምነት ነዉ::

በአራተኛ ደረጃ አንድ ዉል በተለይም ከማይንቀሳቀስ ንብረት ጋር በተያያዘ ሁኔታ የሚደረግ ዉል ሟሟላት ከሚገባቸዉ ቅድመ ሁኔታዎች አንዱ የሆነዉን የዉለታ ፎርም የእነ አቶ ታዲዎስ ስምምነት መጠበቅ እና ሟሟላቱን እናያለን፡፡የፍትሐ ብሔር ሕጉ አንቀጽ 1723 የማይንቀሳቀሱ ንብረቶችን ማለትም መሬትን እና መሬት ላይ በቋሚነት የተተከሉ ንብረቶችን የሚመለከቱ ዉሎችን ሁሉ በጽሑፍና በሚገባ አኳኋን በፍርድ ቤት መዝገብ ወይም ዉል ለማዋዋል ሥልጣን በተሰጠዉ ፊት መመዝገብ አለባቸዉ ሲል አስገዳጅ ቅድመ ሁኔታ አድርጎ ደንግጓል፡፡ስለሆነም በዚህ የሕግ አግባብ ያልተዘጋጁ የማይንቀሳቀሱ ንብረቶችን የሚመለከቱ ስምምነቶች ሕጋዊ ዉጤት አይኖራቸዉም ዉል ተብለዉም አይጠሩም፡፡ከዚህ አንጻር የእነ አቶ ታዲዎስ ስምምነት አይነተኛ የማይንቀሳቀስ ንብረት ከሆነዉ ከመሬት ጋር የተገናኘ በመሆኑ የዉለታዉ ጉዳይ ምንም አይነት ቢሆንም ለሕጋዊነቱ በፅሑፍ መደረግ ብቻ ሳይሆን በዉልና ማስረጃ ምዝገባ ፅ/ቤት መመዝገብ አለበት፡፡ይሁን እንጅ በዉል ሰጭ መሬት ሰጭ የደብሩ ሰበካ ጉባኤ አስተዳደር እና በዉል ተቀባይ በመሬት ወሳጅ አቶ ታዲዎስ ጌታቸዉ መካከል የተደረሰዉ ስምምነት ነገረ ሥሩ መሬት ቢሆንም ጉዳያቸዉ መቀባበል ቢሆንም አግባብነት ባለዉ የዉል እና ማስረጃ ምዝገባ ጽ/ቤት የተረጋገጠ እና የተመዘገበ አይደለም፡፡የመሬትን ጉዳይ ማዕከል ያደረገ ዉል ደግሞ ካልተመዘገበ የሕግ ዕዉቅና እንደሌለዉ እና ረቂቅ ብቻ (a mere draft) ሆኖ እንደ ሚታይ የፍትሐብሔር ሕጉ አንቀፅ 1720(1) በግልፅ ይደነግጋል፡፡ከዚህ አንጻር የእነ አቶ ታዲዎስ ስምምነት መሬትን ማስተላለፍ ሲሆን በሌላ በኩል ግን በዉልና ማስረጃ ምዝገባ ጽ/ቤት ያልታየ ያልተመዘገበ እና ያልጸደቀ በመሆኑ ሕጋዊ ሽፋን የሌለዉ ይልቁንም በሕጉ አጠራር ዋጋ አልባ (void abinition) የሆነ ተራ እና ሕገ-ወጥ ስምምት ነዉ፡፡

ለነገሩ የስምምነታቸዉ ጉዳይ ከመሬት ጋር የተያያዘ በመሆኑ የምዝገባን ቅድመ ሁኔታ አነሳን አንጂ እንዲህ አይነቱን የተጭበረበረ የመንደር ስምምነት የዉልና ማስረጃ ምዝገባ ጽ/ቤትም ሆነ የትኛዉም የመንግስት አካል የዞረበት ካልሆነ በስተቀር ሊያፀድቀዉና ሊመዘግበዉ ቀርቶ ከጅምሩም አይቀበለዉም፡፡ ከሁሉ በላይ የሚያሳዝነዉ ግን የሕግ ሁሉ ምንጭ የሆነችዉ ቤተ ክርስቲያን አለማዊዉንም ሆነ መንፈሳዊዉን ሕግ ጠንቅቀዉ የሚያዉቁ ልጆች ያሏት ቤተ ክርስቲያን፤ ሊሰጧት እንጅ ሊቀሟት የማይገባት ቤተ ክርስቲያን በምስራቅ ሸዋ ሀገረ ስብከት እና በባቦጋያ ምስራቀ ፀሐይ መድኃኒአለም ቤተ ክርስቲያን እንዲሁም በኩሪፍቱ ሪዞርትና ስፖ ማሕተሞች ብቻ በደመቀ ታራ የመንደር ስምምነት መነሻነት መብቷን መገፈፏ እና ጥቅሟን መነፈጓ ነዉ፡፡ሰዎች ማለትም ግለሰቦች እና ተቋመት በማኅበራዊ ኑሮ ዉስጥ ባላቸዉ የእርስ በእርስ ግንኙነት የገንዘብ እና የንብረት ጥቅሞቻቸዉን የተመለከቱ ኢኮኖሚያዊ ግንኙነቶችን እንዲኖራቸዉ እሙን ነዉ፡፡ ስለሆነም የዉል መሠረታዊ ዓላማም አስተማማኝ በሆነ ኢኮኖሚያዊ ግንኙነቶችን (secured transaction) መፍጠር ነዉ፡፡ከዚህ በመነሳት ሰዎች እንደ ፈቃዳቸዉ ያለማንም ጣልቃ ገብነት በመካከላቸዉ አስገዳጅ ስምምነቶችን ለመፍጠር ወይንም ዉል ለመዋዋል ሙሉ ነፃነት ቢኖራቸዉም ግንኙነታቸዉን አስተማማኝ ለማድረግ እና ለስምምነታቸዉም አፈፃፀም ዋስትና ለመስጠት ሕግ የሚያስቀምጣቸዉ ቅድመ ሁኔታዎች እና ገደቦች አሉ፡፡ስለዚህም ሰዎች የሚያደርጓቸዉን የዉል ስምምነቶች በዉል ሕግ ማቀፍ አግባብነት የተቃኙ ሊሆኑ ይገባቸዋል፡፡ያለዚያ ግን ዉል ለመዋዋል መብት ስላላቸዉ ብቻ ማንኛዉንም አይነት ስምምነት ከዉል ሕጉ ድንጋጌዎች በተቃራኒ ቢፈፅሙ ግንኙነታቸዉ አስተማማኝ እና ዉጤታማ አይሆንም፡፡ይልቁንም በስምምነቱ ፈፃሚዎች መካከል የተዛባ ግንኙነት እንዲፈጠርና ከመንግስትና ከሌሎች ሶስተኛ ወገኖች ጋር የጥቅም ግጭት እንዲኖር ያደርጋል፡፡አልፎ ተርፎም ሥርዐት አልበኝነትን ያሰፍናል፡፡

ከዚህ አንፃር የእነ አቶ ታዲዎስ ዉል ከኢትዮጵያ የፍትሐብሔር ሕግ ማዕቀፍ ዉጭ የሆነ ተራ የመንደር ዉል ስምምነት ሆኖ ሳለ የምስራቅ ሸዋ ሀገረ ስብከት ስምምነቱን አይቶ ጉዳዩን መፍቀዱ ይልቁንም የቢሾፍቱ ከተማ መስተዳድር ይህንኑ ሕግ የማይቀበለዉን ስምምነት መሰረት በማድረግ የቤተ ክርስቲያንቱን ሕጋዊ ይዞታ በሕገ ወጥ መንገድ ለአቶ ታዲዎስ ጌታቸዉ አሳልፎ መስጠቱ አግባብነት የሌለዉ እና የሚያሳዝን ጉዳይ ነዉ፡፡ሕግን ያልተከተለ አሰራር እና ሕጋዊ ሽፋን የሌለዉን ስምምነት የግል ጥቅምን ከማስጠበቅ የሚመነጭ ነዉ፡፡የእነ አቶ ታዲዎስም ስምምነት ሕገ-ወጥነቱ እንደ ተጠበቀ ሆኖ የባለሀብቱን የግል ጥቅም ማስከበር ላይ ብቻ ያተኮረ መሆኑን ከፅሑፉ በቀላሉ መረዳት ይቻላል፡፡ለምሳሌ በስምምነቱ የመጀመሪያ አንቀጽ ዉስጥ ቦታዉ በሕጋዊ መንገድ በካርታና ፕላን ሰነድ የተረጋገጠ እንደመሆኑ ሁሉ የሚል የመንደርደሪያ ሀሳብ ሰፍሯል፡፡በዚሁ አንቀጽ ዉስጥም ወረድ ብሎ ዉል ተቀባዩ አቶ ታዲዎስ ቦታዉን ለልማት ስለፈለጉት የከተማዉን ማዘጋጃ ቤት ፈቃድ ለማግኘት በክትትል ላይ የሚገኙ መሆኑን ይጠቅሳል፡፡

 ሁለተኛዉ አንቀጽ ዉስጥ ደግሞ የቦታዉ ይዞታ ይፀድቅልናል የሚል የመብት ጥያቄ ለማንሳት አስፈላጊ ሆኖ ባይገኝም በማለት ያትታል፡፡እንግዲህ ልብ በሉ እነዚህን የዉል ቃሎች ፈቅደዉና ተስማምተዉ በስምምነት ፅሑፍ ዉስጥ በዚህ መልኩ እንዲሰፍር ያደረጉት የወቅቱ የደብሩ አስተዳዳሪና ከእርሳቸዉ ጋር የነበሩ የሰበካ ጉባኤ አባላት ናቸዉ፡፡ከእነዚህ የዉለታ ቃላት እንደምንረዳዉ የስምምነቱ ዉል ሰጭ የነበሩት የወቅቱ የቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ ተወካዮች ይዞታዉ ለቤተክርስቲያን አያስፈልግም ስለዚህም ለቤተክርስቲያንቱም የይገባኛል እና የሕጋዊነት ማረጋገጫ ጥያቄ አናቀርብም የሚል አቋም እንዳላቸዉ ግልፅ ነዉ፡፡ታድያ እንዲህ አይነቱ አቋም በግል እና በስዉር በመጠቃቀም ላይ የተመሰረተ እንዲሁም ከመደራደር አቅም አኳያ ቤተ ክርስቲያኒቱን ያለ ምንም ተነፃፃሪ ጥቅም የጎዳ እና ባለ ሃብቱን አቶ ታዲዎስ ጌታቸዉን ደግሞ ያለ አንዳች ተነፃፃሪ ተጨባጭ ግዴታ ያለ አግባብ ያበለፀገ መሆኑን መረዳት አያዳግትም፡፡

በሌላ መልኩ የቢሾፍቱ ከተማ መስተዳድር የመሬት ክፍል የኢፌዲሪ ሕገ መንግስት አንቀጽ 40(3) ላይ መሬት የማይሸጥ የማይለወጥ የኢትዮጵያ ሕዝብና መንግስት ንብረት ነዉ የሚለዉን ሕገ መንግስታዊ ድንጋጌ በሚቃረን አኳኋን ዉድ የሀገር ሀብት የሆነዉን መሬት ግልፅነት በጉደለዉ እና ሕጋዊ ሽፋን በሌለዉ አሰራር የቤተ ክርስቲያኒቱን መሬት ያለምንም ቅድመ ማስጠንቀቂያ እና ያለምንም የካሳ ክፍያ እንዲሁም ምንም አይነት ተለዋጭ ቦታ ባለመስጠት በደፈናዉ ለባለሃብቱ ለአቶ ታዲዎስ መሬቱን በመስጠት የይዞታ ማረጋገጫ ሰነድና የግንባታ ፈቃድ በመስጠት ሀላፊነት የጎደለዉንሥራ ሠርቷል፡፡ማንኛዉም የመንግስት አስተዳደር ክፍል ግልጽነት የተላበሰ እና ሕግና ሥርዓትን መሰረት ያደረገ ቀልጣፋ አሰራር እንዲኖረዉ ይጠበቃል፡፡ይሁን እንጂ የቢሾፍቱ ከተማ አስተዳደር ማዘጋጃ ቤት ከመሬት ጋር በተያያዘ መልኩ የተፈፀመዉን እና የዉልና ማስረጃ ምዝገባ ጽ/ቤት ያላፀደቀዉን እና ያልመዘገበዉን የእነ አቶ ታዲዎስን የመንደር ዉል መሰረት በማድረግ የመሬት ባለይዞታነትን ማስተላለፍ ብልሹ አሰራር መንገሱን የሚያመለክትና በመንግስትም ላይ ሕጋዊ ተጠያቂነትን የሚያስከትል መሆኑ ግልፅ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር የፍትሐ ብሔር ሕጉ ስለ ሀብትነት ማስረጃ በሚለዉ ክፍሉ ዉስጥ በአንቀፅ 1196(1) እና (2) ዉስጥ በአስተዳደር ክፍል የተሰጠዉ የይዞታ ማረጋገጫ ሰነድ ከደንብ ዉጭ በሆነ አሰራር ከተሰጠ ወይም የሠነዱ አሰጣጥ መሰረቱ የማይረጋ ጽሑፍ ማለትም ከላይ የጠቀስነዉ የእነ አቶ ታዲዎስ አይነት ዋጋ አልባ የመንደር ዉል የሆነ እንደሆነ የተሰጠዉ የይዞታ ምስክር ወረቀት እንደማይሰራ ይገልፃል፡፡

በዚሁ መሰረት በሕግ ዓይን ዋጋ አልባ በሆኑ ጽሑፎች እና አሰራሮች መሰረት የተሰጡ የይዞታ ማረጋገጫ ሰነዶች አለመሰራታቸዉ ብቻ ሳይሆን ለአስተዳደር ክፍሉ ሊመለሱ የሚገባቸዉና የሚሰረዙ መሆናቸዉን የፍትሐብሔር ሕጉ አንቀፅ1197 (1) ይደነግጋል፡፡በተጨማሪም ከፍትሐብሔር ሕጉ አንቀጽ 1198 እንደምንረዳዉ ከመንግስት አስተዳደር ክፍል ሕገ ወጥ በሆነ አሰራር በተሰጠዉ የይዞታ ማረጋገጫ ሰነድ ምክንያት በይዞታዉ ላይ ንብረት ያፈራ ወይም መብት ያገኘ ሰዉ ለሚደርስበት ኪሣራ መንግስት ሓላፊ ወይም ተጠያቂ ይሆናል፡፡ ስለሆነም በሕግ የበላይነት እና በዲሞክራሲያዊ አሰራር ከታመነ እንዲሁም ያሉትን አግባብነት ያላቸዉን ሕጎች በአግባቡ በመተርጎም በፍትሐዊነት ቢሰራ የቢሾፍ ከተማ አስተዳደር በቤተ ክርስቲያንቱ የብሔራዊ በዓላት ማክበሪያ ቦታ ላይ ለአቶ ታዲዎስ የሰጠዉን የይዞታ ማረጋገጫ ሰነድ መሠረዝ እና መስመለስ አለበት፡፡ ምክንያቱም አቶ ታዲዎስ በመሬቱ ላይ ያገኘዉ የይዞታ ሰነድ በሕግ ፊት ሊፀና በማይችል እና ባልተመዘገበ የመንደር ዉል መሰረት ስለሆነ፡፡አቶ ታዲዎስም በመሬቱ ላይ የባለ መብትነት ማረጋገጫ ሰነድ አግኝተዉ መዋዕለ ንዋያቸዉን ያፈሰሱበት በመሆኑ በዚህ ረገድ የሚደርስባቸዉን ኪሳራ ልብ ካላቸዉና ንጽሕ ዜጋ ከሆኑ ከቢሾፍቱ ከተማ አስተዳደር መጠየቅ ይችላሉ ጉዳዩ ልብ የሚሰጥ ሕጋዊ አሰራር ስላልነበረ አቶ ታዲዎስ ይሄንን ያደርጋሉ የሚል 100 ፐርሰንት እርግጠኞች ነን፡፡ መንግስትም ቢሆን እዉነት ለፍትሕ ቆመ ከሆነ ሕግ ተጥሷል ሕግ ይከበር ሕግ ይዳኘን ያለዉን ንፁህ ሕዝብ እንደ ጌታቸዉ ዶኒ በሚያናፍሱት የዉሸት ፕሮፖጋንድ መነዳትና ወደ እስር ከማፈስ ትቶ በዚህ ግልፅነት በጎደለዉ እና ሕገ-ወጥ በሆነ ምስጢራዊ አሰራር ተጠያቂነትን ያስከተሉበትን ሙሰኛ ሹማምንቶች እና ሰራተኞች በወንጀልም ሆነ በፍትሐብሔር ሕግ ሊጠይቃቸዉ ይችላል ይገባልም፡፡

1.2 በቃለ ዓዋዲዉ ዉሉ ሲተነተን

ሰኔ 2/1999ዓ.ም የተወሰነዉ ዉሳኔ ከቃለ ዓዋዲ አንፃር

 የመጀመሪዉ ስምምነት በቃለ ዓዋዲዉ ምዕራፍ 2 አንቀጽ 6 ንዑስ አንቀጽ 7 መሰረት ያደረገ እና ቤተ ክርስቲያኗን እራሷን ማስቻል በሚል ነዉ፡፡ከቃለ ጉባኤ ለመረዳት እንደተቻለዉ የአጥቢያዉ ሰበካ ጉባኤዉ በምዕራፍ ሦስት አንቀጽ 12 ንዑስ አንቀጽ 7 በተራ ፊደል ሀ. ዉል መዋዋልና ሐ. ለሥራዉ በሚያስፈልገዉ መጠን የሚንቀሳቀስና የማይንቀሳቀስ ንብረት በዉል ማከራየትና መከራየት በሚል በተሰጠዉ ስልጣን መሰረት በተጨማሪ ንዑስ አንቀጽ 8 እና 9 በሀገረ ስብከቱ ፈቃድ መሆኑ እንዲሁ በደፈናዉ ሲታይ በዚህ መልኩ ስህተት ቢሆንም መልካም ነዉ፡፡

ሰኔ 10/1999ዓ.ም የተደረገዉ የዉል ስምምነት
ከላይ በቃለ ዓዋዲዉ ላይ የተገለጻዉን የሚጻረር ነዉ በቃለ ዓዋዲዉ ስለ ቤተ ክርስቲያን ይዞታ በግልጽ የተቀመጠ ነገር ባይኖርም ስምምነቱ ግን ምዕራፍ 2 አንቀጽ 5 የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ዓላማ ዉስጥ በንዑስ አንቀጽ 1 ና 4 ላይ የተገለጸዉ ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ለመጠበቅና በማንኛዉም ነገር ራሷን ለማስቻል የሚለዉን ዓላማ የሳተና የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ተግባር የሚለዉን አንቀጽ 6 ንዑስ አንቀጽ 7 ና 8 ቤተ ክርስቲያንን በሀብትና በንብረት በኩል ራሷን ማስቻል ፣የቤተ ክርስቲያን ሀብትና ንብረት እንዳይባክን እየተመዘገበ እንዲጠበቅ ፣ ኢንዲለማና እንዲያድግ ማድረግ የሚለዉን ወደ ጎን የተወና በተቃራኒ መንገድ የቆመ ነዉ፡፡

በዉል ስምምነቱ ላይ የተጠቀሰዉ የቃለ ዓዋዲ ቁጥር 32 የወረደ ጠቅላላ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ አባላት የሚገልጽ ሲሆን ቁጥር 33 የተባለዉም የወረዳ ጠቅላላ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ሥልጣንና ተግበር መሆኑን እና ቁጥር 40 የተባለዉም የመንበረ ዽጵስና ሀገረ ስብከት ጠቅላላ መንፈሳዊ ጉባኤ ሥልጣንና ተግባር የሚገልጽ ሲሆን በአጠቃላይ ስምምነቱ የተጭበረበረ ከቃለዓዋዲዉ ዉጭ የተደረገ ዉል መሆኑን ያሳያል፡፡ የሚገርመዉ ነገር ዉሉ የተጭበረበረ መሆኑ ብቻ ሳይሆን በየደረጃዉ ያሉት የቤተ ክህነት ሰዎች አቡነ ጎርጎርዮስን ጨምሮ በቃለ ዓዋዲዉ መሰረት አለመስራታቸዉና ‹‹ስህተት ነዉ›› ያለዉን ሕዝብ በመወንጀል ስህተታቸዉን ከእግዚአብሔር ይሰወር ይመስል ለመሸሸግ ዛሬ ንጹሕንና ከእነሱ ተሽሎ የቤተ ክርስትያንን መብት ለማስከበር ደፋ ቀና የሚለዉን ክርስቲያን በእስር ቤት ማሳሰራቸው ነው፡፡

‹‹ናቡቴ የአባቶቼን ርስት እሰጥህ ዘንድ እግዚአብሔር ያርቅልኝ››  ብሎ ሳይፈራ ንጉሱ አክአብን ሲመልስለት አቡነ ጎርጎርዮስ ግን የአባቶቻቸዉን ርስት ይሁዳ ጌታን እንዳስማማ የቤተ ክርስቲያንን ህዝቡ ከጉሮሮዉ ቆርሶ የሰጠዉን ከቤተ ክርስቲያን ቆርሰዉ ለባለሃብት ሰጡ፡፡ለዚህም ነዉ መሰለኝ ሰበካ ጉባኤ 13020ካሬ ሜትር በነጻ መስጠቱ ሳያንሰዉ ለአቡነ ጎርጎርዮስ ደግሞ በ2/10/2000ዓ.ም የሚሊኒየሙ ሽልማት አድርጎ 1000ካሬ ሜትር እጅ መንሻ የሰጣቸዉ፡፡ይገርማል!!! እነ አቶ ታዲዎስም በትዉልድ ሀገራቸዉ አርሲ ዞን በቆጅ አካባቢ ሌሙ ማርያምን እንሰራለን እያሉ በድፍረት በልማት ኮሚቴነት ስም ተጠግተዉ የልጇን የመድሀኒዓለምን 13020ካሬ ሜትር በነጻ ወሰዱ፡፡እዉነት በትዉልድ ቦታቸዉ አርሶ አደሩን እንዲሁ ከአንዳንድ  የመንግስት ባለሥልጣን ጋር ተመሳጥረዉ በማፈናቀል ከአባታቸዉ ከባራንበራስ ጌታቸዉ እንደተማሩት አርሶ አደሩ ለዘመናት ግብር እየገበረ ሲጠቀምበት የነበረዉን ከ1000ሄክታር መሬት አፈናቅለዉ የወሰዱት በአርሶ አደሩና ጥረትና በኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት (አባዱላ) ፈቃድ መሬታቸዉን ማስመለስ ችለዋል፡፡አሁን መድሀኒዓለም ባለቤቱ በጅራፍ እየገረፈ እንደሚያወጣቸዉ ተስፋ እያደረግን በ18/07/2004 ዓ.ም የቋሚ ሲኖዶሱ ዉሳኔ ነዉ በማለት አቡነ ጎርጎርዮስ ለአደአ ወረዳ ቤተ ክህነት የላኩትንና ዛሬ አቶ ጌታቸዉ ዶኒ እንደመነሻነት ተጠቅሞት ሕዝቡን በሚያውክበት ዉሳኔ ላይ የባለሙያ አስተያት እንሰጥበታለን፡፡

እንደሚታወቀዉ ዉሳኔዉ በ23/7/2004 ዓ.ም ከደርግ መንግስት በተሻለ መልኩ አንባገነን በሆነዉ በአቶ ጌታቸዉ ዶኒ ለሕዝቡ ትዕቢት በተሞላ መልኩ የተነበበበት ሙሉ ቪሲዲዉ በሰረት በማድረግ  አስተያት እንስጥበት፡፡ በመጀመሪያ ወሳኔዉ ግልፅነትና ፍጥሀዊነት የጎደለዉ በተአምር ከአንድ ዉሳኔ ሰጭ አካል የማይጠበቅ በአድሎና ወገናዊነት የተሞላ ዉሳኔ ነዉ፡፡በቃለ ዓዋዲዉ አንቀጽ 44 ንዑስ አንቀጽ 8 ላይ በተገለፀዉ መሰረት በሀገረ ስብከቱ ክልል ዉስጥ በመጀመሪያ ደረጃም ሆነ በይግባኝ የሚቀርበዉን የሕግና ሥነ ሥርዓት ጉዳይ በሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት እንዲታይ ያደረጋል፡፡ይግባኝ የሚጠየቅበት ጉዳይም ለጠቅላይ ቤተ ክህነት ወይም ለቅዱስ ሲኖዶስ እንዲተላለፍ ያደርጋል፡፡በተጨማሪም አንቀጽ 52 ‹‹የፓትርያርክ ሥልጣንና ተግባር››  በሚለዉ ስር ቁጥር 3 መሰረት መከናወን የነበረበት ሲሆን አጣሪ ኮሚቴዉ ያቀረበዉ የዉሳኔ ሃሳብ እንጂ የተሰጠዉን የማጣራትና አቤቱታዉ ትክክል ነዉ ትክክል አይደለም የሚለዉን አይገልጽም፡፡በሌላ በኩል ደግሞ የችግሩ መንስኤ ሳይገለጽ የተፈጠረዉን ችግር ብቻ  ወገናዊነትና ለባለሃብት ዘብ በመቆም ከአባቶቻችን በማይጠበቅ መልኩ በመግለጽ ጉዳዩ ሃይማኖታዊ ሆኖ እያለ ከመንግስት ጋር ለማጋጨት ፖለቲካዊ ጉዳይ አድርጎ ለማቅረብ የተደረገ ሴራ መሆኑን ከዉሳኔ ሀሳብ መረዳት ይቻላል፡፡

ለዚህ ማስረጃዉ ደግሞ አቶ ጌታቸዉ ዶኒ ዉሳኔዉን ባነበበት ወቅት ኣባቶች አይሳሳቱም የመጨረሻ ዉሳኔ ነዉ በሰላም ብትቀበሉ ይሻላችኋል ዉሳኔዉ ይግባኝ የለዉም በማለት እያስፈራራና ዛሬ የመንግስት ባለልጣናት ችግሩን ከስረ መሰረቱ ሕዝቡ ጋራ ሄዶ ማጣራት ሲገባቸዉ በታሪክ የማይረሳ ጠቅላይ ሚንስቴሩ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ስለ ፍትሕ ከሰጡት መልስ ጋር የሚጋጭ ስራ እየሰሩ ይገኛሉ፡፡በአጠቃላይ በፍትሐ-ብሔር ሕግና ሕገ መንግስት አንዲሁም በቃለዓዋዲዉ ሲታይ ተቀባይነት ያሌለዉን ዉል ትክክል እንደሆነ በማሰብ  እንዲፈጸም ከባለሃብቱ ወገን ወግኖ የሚሯሯጥ የቤተ ክርስቲያን ማዕረግ ያለዉ ሰዉ እዉነት ትክክለኛ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እምነት ተከታይ ነዉ ? መልሱን ለእናንተ፡፡

እንግዲህ ዉሉ ከሕገ መንግስቱና ፍትሐብሔር ሕጉ እንዲሁም ቃለ ዓዋዲዉ አንፃር ምንም አይነት አግባብነትና ትክክለኛነት ይልቁንም የአጥቢያዉን ምእመናንና ቤተ ክርስቲያንቱን መብት የተጋፋ ሆኖ እያለ አቡነ ጎርጎርዮስም በቀን 2/10/2000ዓ.ም በተፃፈላቸዉ የ1000 ካሬ ሜትር የመሬት ስጦታ እንደ እጅ መንሻ ሊወስዱ ከአንድ ጳጳስ አይደለም ተራ ምእመን እንኳን የማይጠበቀዉን ከአንዳንድ ግብረ አበሮቻቸዉና አድር ባይ የመንግስት ባለስልጣናት ጋር በግል ቅዱሳን ሲሞቱላት የነበረችዉን  ቤተ ክርስቲያን አሳለፍዉ የሸጡት ብሎም በአቃቂ ቃሊት ክፍለ ከታማ በአቃቂ መድሀኒዓለም ቤተ ክርስቲያን በአስተዳዳሪነት ተመድቦ ሲሰራ በነበረበት ወቅት ሕዝብን በመከፋፈልና ከመንግስት ጋር በማጋጨት ብሎም የመንግስት ተሻሚዎችን ሲዘልፍ ብሎም የመካነ ኢየሱስ አባልና የግሉን የእምነት ድርጅት አቋቁሞ ሲንቀሳቀስና ለቤተ ክህነት ጭምር አልታዘዝም ብሎ ሲያስቸግር የነበረዉን ቀኝ እጃቸዉ ላይ አድርገዉ ዛሬ የዋሁንና ንጹህን ሕዝብ ለምን እኔ የሰራሁትን ስህተት አነሳ ? በማለት ሃይማኖታዊ ጥያቄ በማንሳቱ የፖለቲካ ጉዳይ አላቸዉ በማለት እንዲጠብቁት የተሾሙትን ሕዝብ ሊታሰሩለት ሲገባ ማሳሰራቸዉ ከወዴት ወገን እንደሆኑ በግልፅ ያስመሰከሩበት ክስተት መሆኑን ተረድተናል፡፡

መንግስት ሕግ ይዳኘን ፤ ሰብአዊ መብታችን ተነክቷል ብሎ ወደ ሕግ አቤት ያለዉን ሕዝብ ማሰሩ በእዉነት ሕገ መንግስታዊ ሆኖ ነዉ ወይስ አቡነ ጎርጎርዮስ——————-አቶ ታዲዎስ ደግሞ———-ስለሆኑ ነዉ? በሚቀጥለዉ ደግሞ ችግሩ መፍትሔ ያገኝ ዘንድ በምዕመናኑ የተወሰደና የተከሄደባቸዉ መንገዶች ይዘን እንቀርባለን

‹‹እዉነትን ግዛት እንጅ አትሽጣት›› ምሳሌ 23፡23

Advertisements

About andadirgen1

አንድ አድርገን

Posted on April 30, 2012, in ወቅታዊ ጉዳይ. Bookmark the permalink. Leave a comment.

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: