እርስ በርሳችሁ የምትበላሉና የምትነካከሱ ከሆነ ግን እርስ በርሳችሁ እንዳትተላለቁ ተጠንቀቁ

From http://www.fetehe.com

‹‹እርስ በርሳችን እንዋደድ የምትል ከመጀመሪያ የሰማችኋት መልእክት ይህች ናት። ከክፉ ወገን እንደሆነ ወንድሙንም እንደገደለው እንደ ቃየል አይደለም ስለምን ገደለው? የእርሱ ሥራ ክፉ የወንድሙ ግን ፅድቅ ስለነበር ነው›› ዩሐ. መልእክት ም.3 ቁ.11 ኢየሱስ ክርስቶስ በመዋዕለ ሥጋው ለትውልድ ካስተማራቸው መልካም ነገሮች መካከል አንዱ ፍቅር ነው። የሁሉ ነገር ማሰሪያ ያደረገው የሰው ልጆችን የእርስ በርስ መተሳሰብና መፈቃቀር ነበር። የክርስትና እምነት ብቻም ሳይሆን በአለም ላይ ያሉ እምነቶች ዋነኛው መሰረታቸው ፍቅር ነው።

ከምንም ነገር በላይ የወንድሞች እርስ በርስ መፈቃቀር ለአገር ግንባታ ዋነኛው መሰረት ነው። የሰው ልጅ በተፃፈ ህግ ብቻ ይኖራል ማለት ያዳግታል። ለዚህ ደግሞ ህግ ከመኖሩ በፊት የሰው ልጆች ያሳለፉትን የትስስሮሽ ኡደት መመልከቱ በቂ ነው፡፡ ከህግ በላይ የሚገዛን እርስ በርስ የምናዳብረው መከባበር ነው። ህዝቦች የአንድ አገር ዜጋ ነን ብለው እንዲያሰቡ ከሚገፋቸው ምክንያቶች ዋነኛው በመካከላቸው የገነቡት የወገንተኝነትና የተቆርቋሪነት ስሜት ነው። አገር ተራራው፣ ሸለቆው፣ ውሃው፣ እንስሳቱ፣ ብቻ አይደለም። በእነዚህ ሁሉ ተፈጥሮዎች ላይ የሚሰለጥን የበላይ የሆነ ፍጥረት አለ። አገር ሰውም ጭምር ነው። አገሬን እጠላለሁ የሚል ግለሰብ ግዑዝ የሆነውን መሬት እጠላለሁ ማለቱ እንዳልሆነ ልብ ልንል ይገባል። የሚጠላው በአጠቃላይ ወንድሞቹንና እህቶቹን ነው።

ስለዚህ ኢትዮጵያ ስለምትባል አገር ስናስብ ኢትዮጵያውያን ስለተባሉ ወንድሞቻችን እና እህቶቻችንም ጭምር እያሰብን መሆን አለበት። አገሬን እወዳለሁ የሚል ግለሰብ በሙሉ በእነዚህ ወገኖች ላይ በሚደርሰው ማናቸውም በጎም ይሁን መጥፎ ተሞክሮዎችን በጋራ እጋራለሁ ለማለት የተዘጋጀ መሆን ይገባዋል። በወንድምነትና በእህትነት ለመተዛዘንና ለመተሳሰብ የግድ ከአንድ እናትና ከአንድ አባት መወለድ አይጠበቅብንም። ሃይማኖትም የወዳጅነታችን ድንበር ከለላ መሆን የለበትም። አገር ሃይማኖት ከሚያስተሳስረው የበለጠ ከተለያዩ ሰዎች ጋር አንድነትን የሚያጋራን የጋራ ቤታችን ነው።

እግዚአብሔርም ለይታችሁ የዚህን እምነት ተከታይ ከዚህ ቤተሰብ ለተወለደ፣ የዚህ ዘር የሆነ፣ ይህንን ቋንቋ ለሚናገር ግለሰብ ወይም ቡድን አድሉ አይልም። ሰው ሁሉ በእግዚአብሔር አምሳል እስከተፈጠረ ድረስ ፍቅራችንን ለሁሉም ዜጋና ወገን ሳንሰስት ልንሰጥ ይገባናል። መጽሀፍ እንዲል ‹‹ወንድሙን የሚጠላ ሁሉ ነፍሰ ገዳይ ነው››፡፡ ክርስቶስ ለሰው ልጆች ሁሉ ሲል ነው እራሱን አሳልፎ የሰጠው። ለይቶ ለእዚህ አገር ዜጐች ብቻ ቤዛ ልሆን መጣሁ አላለም። ምድር የናቀቻቸውን ሁሉ መረጠ። በከብቶች በረት ተወለደ። እንደ ማንኛውም ተራ ዜጋ አደገ።

ጊዜው ሲደርስ አላማውን ከግብ ያደርሱለት ዘንድ በማህበረሰቡ ዘንድ የተናቀ ስራን ይሰራሉ የሚባሉትን ግለሰቦች ለታላቅ ሃዋርያዊ ተልዕኮ አጫቸው፡፡ ወደ እየሩሳሌም ሲገባ የአህያ ውርንጭላን መረጠ። እምነት፣ ተስፋ፣ ፍቅር እነዚህ ሁሉ በሰዎች ዘንድ ይኖራሉ። ከሁሉ ግን ፍቅር እንደሚበልጥ በመፅሐፍ ቅዱስ ላይ እንደተገለፀ ስንቶቻችን እናውቅ ይሆን? ሰዎች እግዚአብሔርን ወደ ላይ አንጋጠው ይፈልጉታል። በየቤተመቅደሱ፣ በየአምልኮ ስፍራ ሁሉ በፀሎት፣ በምልጃ ይተጋሉ። የእምነት ተቋማት የሚጠቀሙባቸውን መባ ያቀርባሉ። ለእምነታቸው ሲሉ ክፈሉ የተባሉትን ዋጋ ሁሉ ለመክፈል ዝግጁ ናቸው። እግዚአብሔር ግን ይላል ስራብ አብልታችሁኛል፣ ስጠማ አጠጥታችሁኛል፣ ስታረዝ አልብሳችሁኛል፣ ስታሰር ጠይቃችሁኛል ይላል። ክርስቶስን የት ነው የምናበላው? የትስ ነው የታሰረው? ልብስ የት ነው የምናመጣለት? ቤተመቅደስ ውስጥ ነው? የተለየ አድራሻ አለው? ምንስ ማለት ነው? አገራችን የቁስ ደሃ ለመሆኗ እንደገና አንስተን አንነጋገርም። ህፃናት በቤተሰብ ችግር ምክንያት ጐዳና ላይ መውደቃቸውን ለማወቅ ማስረጃ መደርደር አይጠበቅብንም። ቀን በፀሐዩ ሀሩር፣ ማታ በብርድ ቁር በየበረንዳው የሚሰቃዩ ወገኖቻችን ስፍር ቁጥር የላቸውም። እነዚህ ወገኖቻችን አይደሉምን? ማን ነው ከወደቁበት አስከፊ ኑሮ የሚታደጋቸው? ማን ያብላቸሁ? ማንስ ያጠጣቸው? የመጠለያውስ ነገር የማን ኃላፊነት ነው ብለን እንተወው? ወንድሞቻችን፣ እህቶቻችን ተቸግረው አይናችን እያየ እንዳላየ አልፈን በቤተመቅሱ እግዚአብሔርን ለመፈለግ የምንገባው የቱን እግዚአብሔርን ነው። እርሱ እኮ በደጅ የሚያበላው አጥቶ የሚለበሰው ቸግሮት ችግሮች በደጅ ተሰቃየቷል። በቱቦ ውስጥ መኖር በራሱ ስቃይ ሆኖበታል። የሚታየውን እግዚአብሔርን ትተን የማይታየውን አምላክ ለመፈለግ መታተራችን ያለማስተዋል ውጤት ነው። ፍቅር ቢኖረን ኖሮ እግዚአብሔርን ባወቅነው ነበር። መጽሐፍ እንዲህ ይላል ‹‹የዚህ አለም ንብረት ያለው ወንድሙንም ተቸግሮ አይቶ ምፅዋትን ቢከለክለው እግዚአብሔርን እንዴት ያውቃል?››። እግዚአብሔርን ማወቅ እንግዲህ እንዲህ ነው። ለገዛ ወገን ማድላት ግዴታ እንጂ የሞራል ሀላፊነት ብቻ አይደለም። የራስ ወዳድነትም አንዱ መገለጫ ከዚሀ ሀሳብ ጋር መቃረን ነው። ወንድሞችን ለማገልገል የግድ በደም መወራረስ የለብንም። ፍቅር

ካለ ሁሉም ነገር ይቻላል። ግማሸ የሚሆኑት የአገራችን የማህበረሰብ ክፍል (በጐዳና ላይ የወደቁትን ችግረኛ ህፃናት እና አዛውንቶች) ማሰብ ብንችል ኖሮ አገራችን የጐዳና ተዳዳሪም ይሁን በልቶ ማደር ያቃታቸው ዜጐች መኖሪያ ባልሆነችም ነበር። ፍቅር የሌለው ማህበረሰብ እርስ በርሱ አይስማማም። ችግሮችን ለመፍታት ከመስማማት ይልቅ ለፀብ ይዳረጋል። በዚህም የአገር ህልውና አደጋ ላይ ይወድቃል። ኢትዮጵያን ለመገንባት ኢትዮጵያዊነት የሚለውን ጠንካራ የጋራ መንፈስ መገንባት የግድ ያሻል። የአገር አንድነት ግዑዝ በሆነው መሬት ላይ አይገነባም። የአገር ምንነት በሰዎች ልቦና ውስጥ የሚተሳሰር የመንፈስ አንድነት ነው። መንፈሱ ከአገሩ የራቀን ሰው የግድ የአገር ባለቤትነትን ልንሰጠው አንችልም። ኢትዮጵያዊ ነህ ብሎም ማስገደድ አያዋጣም። እንዲህ አይነት አካሄዶች አገርን ከመበታተን ውጭ ህልውናዋና ሲታደጋት አልተመለከትንም። ከኢትዮጵያ የተገነጠሉትም ይሁን አሁንም መገንጠል የሚፈልጉ ቡድኖች መንፈሳቸው ከአገር ምንነት ስለራቀባቸው ውጭ ውጭውን ተመኝተው ጉዳያቸውን አሳክተዋል ከፊሉም እየሞከረ ይገኛል።

የአገር አንድነትን የማይደግፉ ሰዎች ምክንያታቸው የፍቅር እጦት ነው። ከሌሎች የህብረተሰብ ቡድኖች ጋር በአንድነት ለመኖር የሚያግዛቸውን አንድነት መመስረት አልተቻላቸውም። እንደተገፉ፣ እንደተረገጡ፣ እንደተበደሉ አሰቡ። ያላቸው አማራጭ ሌላ ፍቅር ሊያገኙበት የሚችሉትን የእምነት አንድነት መገንባት ነው። በሌሎች ወገኖች ላይ የሚደርሰው በደልና ስቃይ በኛ ላይ እስካልደረሰ ድረስ ምንም አይመለከተንም ብለን የተቀመጥን ብዙዎቻችን ነን። ደቡብ አፈሪካዊው የመንፈስ አባት ዴዝሞን ቱቱ ‹‹በዳዮችን እንዳላየ የሚያልፍ የበዳይ ተባባሪ ነው›› ብለው ነበር ፍቅራችንን ሸሽተናል። የዚህ ውጤት ደግሞ ያሳለፍናቸው አስከፊ ጦርነቶች እና ጥሏቸው ያለፈው ጠባሳዎች ናቸው። ቅዱስ ጳውሎስ ለገላትያ ሰዎች በላከላቸው መልእክቱ በምዕራፍ 5 ቁ.13-15 የፍቅርን ምንነትና ጦስ እንዲህ ነግሯቸዋል፡- ‹‹ወንድሞች ሆይ እናንተስ ለነፃነት ተጠርታችኋል፣ ነገር ግን በሥጋችሁ ፍቃድ ለነፃነታችሁ ምክንያት አታድርጉለት ለወንድሞቻችሁ በፍቅር ተገዙ። ወንድምህን እንደራስህ ውደድ የሚለው አንድ ቃል ሕግን ሁሉ ይፈፅማልና። እርስ በርሳችሁ የምትበላሉና የምትነካከሱ ከሆነ ግን እርስ በርሳችሁ እንዳትተላለቁ ተጠንቀቁ››__

Advertisements

About andadirgen1

አንድ አድርገን

Posted on June 14, 2012, in ስብከት. Bookmark the permalink. Leave a comment.

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out / Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out / Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out / Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out / Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: